Bayu online
Contact information, map and directions, contact form, opening hours, services, ratings, photos, videos and announcements from Bayu online, Health/Beauty, Ethiopia, Addis Ababa.
26/02/2026
ቅድስት፡ የዐቢይ ጾም ኹለተኛ ሳምንት
በመ/ር ጌታቸው በቀለ
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን የበዓላት ቀኖና መሠረት የዐቢይ ጾም ኹለተኛው ሳምንት “ቅድስት” ይባላል፤ ትርጓሜውም የተቀደሰች፣ የተለየች ማለት ነው፡፡ በዚህ ዝግጅታችን ኹለተኛውን ሳምንት ቅድስትን ስያሜና ምሥጢሩን እንማራለን፡፡
ቅድስት ምን ማለት ነው?
ሊቁ ቅፉስ ያሬድ ለዐቢይ ጾም ኹለተኛው እሑድ በአዘጋጀው ምስጋና አማካኝነት ዕለቱ “ቅድስት” የሚል ሥያሜ ሰጥቶታል፡፡ “ቅድስት” ማለት ፍችው “የተቀደሰች፣ የተለየች፣ የተባረከች፣የከበረች፣ ንጽሕት” ማለት ነው፡፡/መጽሐፈ ሰዋስወ ወግስ ወመዝገበ ቃላት ሐዲስ/፡፡ መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በገዳመ ቆሮንቶስ ገብቶ ከቆመ ሳያርፍ፣ ከዘረጋ ሳያጥፍ የጾማት የአርብዓው ቀንና ሌሊት ልዩ የሆነችና ክብርት ጾም የምትጀመርበትን ኹለተኛ ሳምንት ናት /ማቴ. ፬፥፪/፡፡ «ጾምን ቀድሱ ጉባኤውን ዐውጁ ሽማግሌዎችንና በምድር የሚኖሩትን ሁሉ ወደ አምላካችሁ ወደ እግዚአብሔር ቤተ ሰብስቡ፡፡» /ት.ኢዩ. ፪፥፲፬/ ብሎ በነቢዩ ኢዩኤል አፍ የተናገረ ቅዱስ እግዚአብሔር የጾማት ጾም ስለሆነች ቅድስት ትባላለች። ቅድሰት የዐቢይ ጾም ኹለተኛ ሰንበት (ሳምንት) ስያሜ ነው፡፡ ዕለቱ “ቅድስት” ተብሎ የተሰየመበት ምክንያት የእግዚአብሔር አምላክን ፍጹም ቅድስና የሚያወሳ፣ የሰንበትን ቅድስና የሚያዘክር ምስጋና የሚቀርብበት ሳምንት ነው፡፡ ከዋዜማው ጀምሮ የሚዘመረው ጾመ ድጓ የአምላካችን ቅድስና እና ሰንበትን ቀድሶ በፈቃዱ እንደሰጠን የሚያነሣው ክፍል ነው፡፡ ይህም ከጾመ ድጓው “ይህች ቀን የተቀደሰች ናት፣ ያረፍኩባት ቅድስት ሰንበት ናት እኔ ቅዱስ እንደሆንኩ እናንተም ቅዱሳን ሁኑ፣ አብ ሰንበትን አከበራት፣ ቀደሳት” የሚል ነው፡፡ “ቅድስት” የሚለው ሥያሜም ሰንበት የዕረፍታችን ቀን እንድትሆን በብሉይም በሐዲስም እግዚአብሔር የባረካት፣ የቀደሳት ዕለት መሆኗን የሚያመለክት ነው፡፡ ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችንም ሰንበቱን ስለ ቅድስና ልጆቿን ታስተምርበታለች፡፡
ቅድስት — ዕለተ ሰንበት
ቅድስት የዐቢይ ጾም ኹለተኛ ሳምንት ሲሆን፤ ለጌታ ጾም (ጾመ ዐርባ) የመጀመሪያ ሳምንት ነው፡፡ ለዘመኑ ጥንትና ፍጻሜ ለግዛቱ ዳርና ድንበር የሌለበት ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለእኛ አብነት ይሆነን ዘንድ ጾሙን የጀመረበት የመጀመሪያው ሳምንት “ቅድስት” ተብሎ ይጠራል፡፡ “እግዚአብሔር ሰባተኛይቱን ቀን ባረካት ቀደሳት” /ዘፍ. ፪፥፫፣ ዘጸ. ፳፥፰/ ሰዎች ፍጥረት ያልተፈጠረባት ዕለት ብለው እንዳይንቋት እንዳያቃልሏት ዕረፍተ ሥጋ፣ ዕረፈተ ነፍስ የተገኘባት ዕለት ስለሆነች ቀደሳት አለ፡፡ ቅዱስ ያሬድም በዚህ እሑድ (ሳምንት) ቀደሳት፣ አከበራት፣ ከፍ ከፍ አደረጋት የተባለች ሰንበትን የምትታሰብበት የሰንበትንም ቅድስና የሚመለከቱ መዝሙሮች የሚቀርብበት ሳምንት በመሆኑ ቅድስት ተብሏል።
ከላይ እንደተገለጸው እቀደስ አይል ቅዱስ፤ እከብር አይል ክቡር፤ እነግስ አይል ንግሥና የባህሪዩ የሆነ አምላክ ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ጾሞ፤ የጾምን ጥቅምና ሥርዓቱንም ሊያስተምረን መጾም የጀመረበት ሳምንት ነው ቅድስት፡፡ ይህ ሳምንት የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ የባሕሪይ ቅድስና የሚነገርበት ሳምንት ነው፡፡ ስለዚህች ቀን ነቢየ እግዚአብሔር ቅዱስ ዳዊት አስቀድሞ “የአሕዛብ አማልክት ሁሉ አጋንንት ናቸው፡፡ እግዚአብሔር ግን ሰማያትን ሠራ፡፡ ምስጋናና ውበቱ በፊቱ፤ ቅድስናና ግርማ በመቅደሱ ውስጥ ናቸው፡፡” በማለት ቅድስናና ክብር የባሕሪዩ መሆኑን ተናግሯል/መዝ ፺፭፥፭/፡፡ እኛ ከርኵሰታችን የምንቀደስበትንና የምንከብርበትን ሥርዐት ሊሠራልን አንድም አዳም በመብል ምክንያት ከክብሩ ተዋርዶ ነበርና በአዳም ምትክ ተተክቶ ካሣ ሊከፍልለት በገዳመ ቆሮንቶስ ጌታችን መጾም መጀመሩን በዲያብሎስ መፈተኑንና ዲያቢሎስንም ድል መንሣቱን ቤተ ክርስቲያናችን በዚህ ሳምንት ታስተምረናለች፡፡
እንደ ማጠቃለያ
ይህች ሰንበት “ቅድስት” የተባለችው በባሕርይው ቅዱስ የሆነ አምላካችን እግዚአብሔር ዓለምን ለመቀደስ ሲል ወደ ምድር መምጣቱን፣ የቅድስና አብነት ይሆነን ዘንድም በሥጋው ወራት እንደ ሰውነቱ በጎ ምግባራትን መሥራቱን፣ የቅድስና ተግባር መገለጫ የሆነ ጾምንም መጾሙን ለማስረዳት ነው፡፡ እግዚአብሔር ቅዱስ በመሆኑ የተቀደሰ ነገር ያስፈልገዋልና ሰው ሁሉ በቅድስና መንገድ በመመላለስ የክብሩ ባለቤት የመንግሥቱ ወራሽ እንዲሆን ቤተክርስቲያን ታስተምራለች፡፡
በዚህች ቅድስት ሰንበት በቤተክርስቲያን በመሰብሰብ ቃለ እግዚአብሔር በመስማት (በመማር)፣ ንስሐ ገብቶ ቅዱስ ቍርባን በመቀበል፣ የተጣላ በማስታረቅ፣ ያዘነ የተከዘ በማጽናናት፣ የታሰረ በመጠየቅ በአጠቃላይ በማቴ. ፳፭፥፴፭—፴፯ ላይ የተጠቀሱትን ምግባራትን በመፈጸም ዕለቱን (በዓሉን) ማክበር ከእግዚአብሔር ዘንድ በረከትን ያሰጣል፡፡
የእግዚአብሔር ቸርነት
የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያም አማላጅነት አይለየን፡፡አሜን፡፡
ወስብሐት ለእግዚአብሔር፡፡
ዋቤ መጻሕፍት
✍️ መጽሐፍ ቅዱስ
✍️ መጽሐፈ ድጓ
✍️ መጽሐፈ ግጻዌ
✍️ መጽሐፈ ሰዋስው ወግስ ወመዝገበ ቃላት ሐዲስ
✍️ የቤተክርስቲያን ታሪክ በኢትዮጵያ
Click here to claim your Sponsored Listing.
Category
Website
Address
Addis Ababa